የኤሌክትሪክ ኃይልን ያለ ገመድ በአየር ላይ የሚያስተላልፈው ቴክኖሎጂ

የኤሌክትሪክ ኃይልን ያለ ገመድ በአየር ላይ የሚያስተላልፈው ቴክኖሎጂ


  ስዊድናዊው የቴሌኮምዩኒኬሽን ኩባንያ ኤሪክሰን ፖወርላይት ቴክኖሎጂስ ከተባለው የአሜሪካን ኩባንያ ጋር በመተባበር ለ5ጂ ጣብያዎቹ በብርሃን አማካኝነት ኃይልን በአየር ላይ አስተላልፎ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡


  የኤሌክትሪክን በአየር ላይ ማስተላለፍ ከዚህ ቀደም ያልታየ ቴክኖሎጂ አይደለም፤ አሁን ላይ ብዙዎች ገመድ አልባ የተንቀሳቃሽ ስልክ እና ሌሎችንም ቻርጅ ማድረጊያ መሳርያዎችን በመጠቀም ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም በነዚህ መሳርያዎች ላይ ያለው በአየር ላይ ኃይልን ማስተላለፍያ ቴክኖሎጂ በአጭር እንጂ ረዘም ባለ ርቀት ላይ ለመስራት ይቸገራል፡፡ ታድያ ሁለቱ ኩባንያዎች ይህን ችግር ለመቅረፍ ኦፕቲካል ቢሚንግ የተባለውን ስርዓት በመጠቀም ኃይልን በሚለቀቅ ብርሃን አማካኝነት በማሰራጨትና ኃይሉን የሚቀበለው ጣብያም ይህን በአየር ላይ የሚላክለትን ከፍተኛ ብርሃን ተቀብሎ ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል በመቀየር እንዲጠቀም የሚያደርጉት ይሆናል፡፡


  ሁለቱ ኩባንያዎች ባከናወኑት ሙከራ ኃይልን ከአንድ ኃይል መላክያ ጣብያ 300 ሜትር ርቆ ወደሚገኝ የኤሪክሰን 5ጂ ራዲዮን ጣብያ በመላክ ቴክኖሎጂው ውጤታማ መሆን እንደሚችልም አሳይተዋል፡፡ በሙከራው ላይ 48 ዋት የሚሆን ኃይል የተላለፈ ቢሆንም ኤሪክሰን ግን በዚህ መንገድ የሚተላለፈውን ኃይል እስከ 1 ሺህ ዋት ማድረስ እንደሚቻል ጠቁሟል፡፡ እዚህ ላይ በመብራት አማካኝነት የሚተላለፈው ኃይል ለሰው ልጆችም ሆነ እንስሳት ጤና አስጊ እንዳይሆን በመስጋት ብርሃኑን አቋርጦ የሚያልፍ ሰው ወይም እንስሳ ሲመጣ መለየት የሚችሉ ሴንሰሮች ተካተውበታል፡፡ በዚህም ብርሃኑን አቋርጦ የሚተላለፈው ሰው አቋርጦ እስኪጨርስ ድረስ የሚተላለፈውን ብርሃን በመግታት ጣብያው ለጊዜው በባትሪ ኃይል ብቻ እንዲሰራ የሚያደርጉት ይሆናል፡፡


  ፓወርላይት እንደሚለው ከሆነ ኃይል ተቀባዮቹ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችሉ በመሆናቸው ከ5ጂ ጣብያዎች ባሻገርም እንደ ሙዚቃ ኮንሰርት እና ሰው አልባ ባህር ሰርጓጅ መርከቦች ባሉት ላይ የመዋል አቅም አላቸው፡፡ ሌሎች በበኩላቸው ቴክኖሎጂው የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ቻርግ ለሚያደርጉ ጣብያዎች ኃይል ለማቅረብ፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን የማስተካከል ስራን ቀለል ለማድረግ ወይም በተፈጥሮ አደጋና ጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ላይ ኃይልን በቶሎ ለመመለስ እንደሚያስችል ይገልፃሉ፡፡



@JETAppsHD



Comments